eotcgbg.org

Gothenburg St. Gebriel ETOC

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? ትምህርት እንዴት ነው? በርትታችሁ እየተማራችሁ ነውን? ጥናቱንም ከወዲሁ ጀምሩ! አዲሱን ዓመት ከተቀበልን ሁለት ወራትን አስቆጥረናል፤ ታዲያ በእነዚህ ጊዜያት በዘመናዊ ትምህርታችን ከነበረን ዕውቀት ምን ያህል አዲስ የማናውቀውን ነገር ዐወቅን? አንዳንድ ትምህርት ቤት የሙከራ ፈተና ጀምረዋል፤ ታዲያ እንዴት ነበር የመመዘኛው ፈተና? ጥሩ ውጤት እንዳስመዘገባችሁ ተስፋችን ነው! መልካም!

ባለፈው ትምህርታችን ስለ አማላጅነት በመጠኑ ተምረናል፤ ለዛሬ ደግሞ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንማራለን፤ ተከታተሉን!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የአማላጅነትን ጸጋ የሰጠው (የፈቀደው) እግዚአብሔር ነው፤ ቅዱሳን በተሰጣቸው ጸጋ፣ ቃል ኪዳናቸውን አምኖ በስማቸው ለሚማጸን፣ በስማቸው ለሚዘክር፣ መታሰቢያቸውን ለሚያከብር ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ያማልዱታል! ኃጢአት ሠርቶ ከእግዚአብሔር በተጣላ ጊዜ ተጸጽቶና ይቅርታን ፈልጎ ሲመጣ፣ በቅዱሳን ቃል ኪዳን ሲማጸን ስለቅዱሳን ሲል እግዚአብሔር ምሕረት አድርጎለት ይታረቀዋል፡፡

ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ስለ ቅዱሳን አባቶቻችን እናቶቻችን አማላጅት በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በተአምራት፣ በገድላት መጻሕፍት ብዙ የተጻፉ አሉ፤ ለአብነት ያህል የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትን በቅድሚያ እንመልከት!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እመቤታችን ከተወደደ ከልጇ አማልዳቸው ችግራቸው የተፈታላቸው፣ ጎዶሏቸው የሞላላቸው፣ ኃጢአታቸው ተሰርዮላቸው ከእግዚአብሔር የታረቁ፣ ምሕረትን ያገኙ፣ ብዙዎች ናቸው፤ አንድ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ደግሞ ከተአምረ ማርያም እንመለከታለን፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው በጻፈልን የምሥራች ወንጌል በምዕራፍ ፪÷፩-፲፩ ተጽፎ የምናነበው አንድ ታሪክ አለ፤ ቃና ዘገሊላ በተባለ ቦታ ሠርግ ተደግሶ ብዙ  ሰው ተጠራ፤ በዚያ ሠርግ ላይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ሐዋርያት ተጠርተው ተገኙ፤ የተጠራው እንግዳ ይበላ፣ ይጠጣ ጀመር፤ ይገርማችኋል በጣም ብዙ ሰው ስለነበር ይጠጣ የነበረው የወይን ጠጅ አለቀ! ድግሱን አዘጋጅተው እንግዳ የጠሩ ሰዎች ተጨነቁ፤ ምክንያቱም እንግዶችን “ኑ ብሉ፤ ጠጡ” ብለው ጠርተው ግን አለቀባቸው፡፡

በዚህን ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጭንቀታቸውን አየች፤ ኀዘናቸውን ተመለከተችና ወደ ልጇ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ጠጋ ብላ ‹‹…የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም…›› አለችው፤ ከዚያም ጌታችን ‹‹…ከአንቺ ጋር ምን አለኝ›› አላት…፡፡ ምን ማለት መሰላችሁ? “ልጄ ሆይ አድርግላቸው ብለሽ ብትለምኚኝ አይሆንም እልሽ ዘንድ ከአንቺ ከእናቴ ጋር ምን ጸብ ክርክር አለኝ” ማለት ነው፡፡ ይህ አነጋገር ለእናቱ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ለመግለጽ የተጠቀመበት ነው፡፡

ከዚያም እመቤታችን ወደ ሰዎቹ ሄደችና ‹‹የሚላችሁን አድርጉ›› አለቻቸው፤ ጌታችንም ባዶ የወይን መጥመቂያ ጋን (እንስራ) እንዲያመጡ አዘዛቸው፤ ውኃ ሙሉበት አላቸው፤ እመቤታችን እንደነገረቻቸው የሚላቸውን አደረጉ፤ በጋኑ (በእንስራው) የተሞላው ውኃ ወደ ወይን ጠጅ ተቀየረላቸውና እንግዶቻቸውን አስተናገዱበት፡፡ በእመቤታችን አማላጅነት ጎዶሏቸው ሞላ፤ ድንጋጤአቸው ተወገደ፤ ደስታን ተሞሉ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን ስለእኛ ብሎ ሰዎቹን ከኀዘን፣ ከማፈር፣ ከመጨነቅ ታደጋቸው፤ እመቤታችንም ከልጇ አማልዳ የልባቸውን በጎ መሻት (ፍላጎት) አሟላችላቸው፡፡

ሌላው እመቤታችን በምልጃዋ ምሕረትን ካሰጠቻቸው አንዱ በላዔሰብ (ስምዖን) የሚባል ሰው ነው፤  ይህ ሰው ብዙ ኃጢአትን የሠራ፣ የፈጣሪ የአምላኩን ሕግ ጥሶ ሰዎችን ያሳዘነ፣ ክፉና ጨካኝ ሰው ነበር፤ ታዲያ አንድ ቀን በመንገድ ሲሄድ በጣም የታመመ በዚያ ላይ ደግሞ ውኃ የጠማው፣ የራበውን አንድ ሰው አገኘ፤ ሰውየው ውኃ እንዲሰጠው ‹‹ስለ እግዝእትነ ማርያም›› ብሎ ለመነው!

ይገርማችኋል ልጆች! ይህ ሰው ክፉ ሳይሆን እና ኃጢአት ሳይሠራ በፊት በእመቤታችን ስም ዝክርን የሚዘክር፣ ለተራበው የሚያበላ፣ ደግ ሰው ነበር፤ ከብዙ ዘመናት በኋላ ግን ይሰጥ የነበረው ቀማኛ ሆነ፤ ደግ የነበረው ክፉ ሆነ፤ ለሰው ያዝን የነበረ ሰዎችን የሚያሳዝን ሆነ፡፡

ታዲያ የእመቤታችንን ስም ሲጠራበት ቀድሞ ያደርጋቸው የነበሩ መልካም ሥራዎች ታወሱት፤ ‹‹አሁን ስሟን ስለጠራኽብኝ ስለእግዝእትነ ማርያም ስል እሰጥኻለው›› አለና ከያዘው ኮዳ ጥቂት ውኃ አፉ ላይ ጠብ አደረገለት፤ ግን ሰውየው (የተጠማው) ውኃው ከጎሮሮው ወርዶ ወደ ውስጥ ሳይገባ ሞተ፡፡

ከዚያም በላዔ ሰብእ የተባለው (ስምዖን) ክፉ ሰውም ሞተ፤ በዚህን ጊዜ መልአከ ጽልመት የተባሉ የሰይጣን ሠራዊት ነፍሱን ከሥጋው ከተለየች በኋላ ‹ይህች ነፍስ የእኛ ናት ወደ ሲኦል ነው የምንወስዳት›› አሉ፤ እመቤታችን ደግሞ ‹‹…ይህች ነፍስ የእኔ ናት፤ በስምሽ የዘከረ፣ ስምሽን የጠራ እምርልሻለው ብለኸኛል፤ ይህች ነፍስ በስሜ ስትዘክር፣ የተራበን ስታበላ ነበር፤ በእኔም ስም ለተጠማ ሰው ውኃን አጠጥታለች..›› ብላ ያችን ነፍስ በአማላጅነቷ ሲኦል ከመግባት፣ መከራ ከመቀበል ታደገቻት፡፡ (ተአምረ ማርያም ተአምር ፲፪ ገጽ ፵፫)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አምላካችን እግዚአብሔር ስለ ክብርት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲል ኃጢአታችንን ይቅር ብሎ ምሕረትን ይሰጠናል፡፡ በእርሷ አማላጅነት ታምነን፣ ስሟን እየጠራን ስንማጸን ምሕረትን ያደርግልናል፤ መልካም ምኞታችንንም ይፈጽምልናል፤ ስለዚህም በጸሎቷ፣ በአማላጅነቷ እንዲሁም በተራዳኢነቷ ታምነን መኖር ይገባናል!